Exodus 17

ከዐለት የፈለቀ ውሃ

1መላው የእስራኤል ማኅበር ከሲና ምድረ በዳ ተነሥቶ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው ከስፍራ ወደ ስፍራ ተጕዞ በራፊዲም ሰፈረ፤ ነገር ግን ሕዝቡ የሚጠጡት ውሃ አልነበረም። 2ስለዚህ፣ “የምንጠጣውን ውሃ ስጠን” በማለት ሙሴን ተጣሉት።

ሙሴም፣ “እኔን ለምን ትጣሉኛላችሁ? እግዚአብሔርንስ (ያህዌ) ለምን ትፈታተኑታላችሁ?” አለ።

3ነገር ግን ሕዝቡ በዚያ ተጠምተው ስለ ነበር፣ በሙሴ ላይ አጕረመረሙ። እነርሱም፣ “እኛና ልጆቻችን እንዲሁም ከብቶቻችን በውሃ ጥም እንድናልቅ፣ ከግብፅ ለምን አወጣኸን?” አሉት።

4ከዚያም ሙሴ፤ “በዚህ ሕዝብ ምን ላድርግ? በድንጋይ ሊወግሩኝ ተዘጋጅተዋል” ብሎ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ።

5 እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ እንዲህ መለሰለት፤ “ከሕዝቡ ፊት ሂድ፤ ከእስራኤል አለቆች አንዳንዶቹን እንዲሁም አባይን የመታህባትን በትር ያዝና ሂድ። 6ኮሬብ አጠገብ ባለው ዐለት በዚያ እኔ በአንተ ፊት እቆማለሁ። ዐለቱን ምታው፤ ከእርሱም ሕዝቡ የሚጠጡት ውሃ ይወጣል።” ስለዚህ ሙሴ በእስራኤል አለቆች ፊት ይህንኑ አደረገ። 7ስፍራውንም ማሳህና
ማሳህ ማለት መፈተን ማለት ነው።
መሪባ
መሪባ ማለት መጣላት ማለት ነው።
ብሎ ጠራው፤ እስራኤላውያን ጠብ ፈጥረው፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእኛ ጋር ነው ወይስ አይደለም” በማለት እግዚአብሔርን (ያህዌ) ተፈታትነዋልና።

አማሌቃውያን ተሸነፉ

8አማሌቃውያን መጥተው እስራኤላውያንን ራፊዲም ላይ ወጉ፤ 9ሙሴም ኢያሱን፣ “ከሰዎቻችን አንዳንዶቹን ምረጥና አማሌቃውያንን ለመውጋት ውጣ፤ በነገው ዕለት የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) በትር በእጆቼ ይዤ በኰረብታው ጫፍ ላይ እቆማለሁ።”

10ስለዚህ ኢያሱ ሙሴ ባዘዘው መሠረት ከአማሌቃውያን ጋር ተዋጋ፤ ሙሴ፣ አሮንና ሖርም ወደ ኰረብታው ጫፍ ወጡ። 11ሙሴ እጆቹን ወደ ላይ በሚያነሣበት ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያን ድል ያደርጉ ነበር። እጆቹን ባወረደ ጊዜ ግን አማሌቃውያን ያሸንፉ ነበር። 12የሙሴ እጆች እየዛሉ በሄዱ ጊዜ ድንጋይ ወስደው ከበታቹ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሖርም አንዱ በአንዱ በኩል ሌላውም በሌላ በኩል ሆነው እጆቹን ወደ ላይ ያዙ። ይኸውም እጆቹ ፀሓይ እስክትጠልቅ ድረስ ጸንተው እንዲቈዩ ነው። 13ስለዚህ ኢያሱ የአማሌቃውያንን ሰራዊት በሰይፍ ድል አደረገ።

14ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ሲታወስ እንዲኖር ይህን በጥቅልል መጽሐፍ ላይ ጻፈው፤ ኢያሱም መስማቱን አረጋግጥ፤ ምክንያቱም የአማሌቃውያንን ዝክር ከሰማይ በታች ፈጽሜ እደመስሳለሁ” አለው።

15ሙሴም መሠዊያውን ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) አርማዬ ነው” ብሎ ሰየመው። 16“እጆች ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዙፋን ተዘርግተዋልና፤
ወይም፣ ምክንያቱም እጅ በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ተዘርግቷል…
እግዚአብሔር (ያህ) አማሌቃውያንን ከትውልድ እስከ ትውልድ ይዋጋቸዋል” አለ።

Copyright information for AmhNASV